black blue and yellow textile

ትምህርተ እግዚአብሔር

                         የትምህርቱ ዓላማ

ትምህርቱ የሥላሴን አስተምህሮ ከማሳየቱ ባሻገር በድነት ሥራ ውስጥ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን ድርሻና እንዲሁም በድነት ውስጥ የመለኰትን ዘላለማዊ ዕቅድ ከማሳየቱ በተጨማሪ በአማኝ ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደሚገለጥና እንደሚሠራ ያስገነዝበናል።

ከእውቀት አንፃር

ዳግም ልደት ላይ በመመርኮዝ የሥላሴን ምንነት አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በዘላለማዊ ዕቅድ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ የሚያስገነዝብና የሚያስጨብጥ ነው።

ከውስጣዊ ማንነት /አመለካከት/ አንፃር

ዳግም ልደት ያገኙ ሰዎች የሥላሴን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ተገንዝበው የእግዚአብሔር አብን፣ የእግዚአብሔር ወልድንና፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አንድነትና ሦስትነት እንዲሁም በአንድነታቸው ውስጥ ያላቸውን ድርሻ በማወቅ የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው።

ከክህሎት አንፃር

ዳግም ልደት ያገኙ ሰዎች የሥላሴን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በሚገባ ተገንዝበው ስለ እግዚአብሔር አብ፣ ስለ እግዚአብሔር ወልድና ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች እንዲያስተምሩና እንዲያስረዱ ያስችላቸዋል።

                                                                                                          ትምህርት አንድ

                       ትምህርተ እግዚአብሔር

1. 1. የእግዚአብሔር ሕልውና

ስለ እግዚአብሔር መማር ለድኅነታችን እጅግ ዋና ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው። እግዚአብሔር የሚለው ቃል ለአማርኛችን ምንጩ ግዕዝ ሆኖ “እግዚኦ” ጌታ “ብሔር” ዓለም ማለት ነው። ስለዚህ የዓለም ጌታ የሚል ፍቺ አለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕልውና መሠረታዊ እውነት መሆኑን መነሻ በማድረግ የተጻፈ እንጂ የእግዚአብሔርን መኖር ለማረጋገጥ የተጻፈ አይደለም። ስለሆነም የእግዚአብሔርን ሕልውና በመቀበል ስለ እግዚአብሔር የፈጣሪነት ሥራ በመናገር ይጀምራል /ዘፍ 1፥1/።

የእግዚአብሔርን ሕልውና መካድ የሞኝነት አስተሳሰብ ነው /መዝ 14፥/። የእግዚአብሔርን መኖር ባለማወቅም ይሁን በሞኝነት ወይም ለሚክዱ ሁሉ ሕልውናው የሚታወቅና የተረጋገጠ መሆኑን የእግዚአብሔር ቃል በማብራራት ያስተምራል።

1.1.1. በፈጠረው ፍጥረት

የእግዚአብሔር ሕልውና በፈጠረው ፍጥረት ግልጽ ሆኖ ይታያል። እግዚአብሔር የማይታይ ባህርይ፣ የዘላለም ኃይልና አምላክነት ያለው ነው /ሮሜ 1፥8-21/። ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማያት ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል መዝ19 1-4/። እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረና የፈጠረውን ነገር ሁሉ የሚያውቅ፤ በስማቸውም የሚጠራ፣ በኃይሉና በችሎቱ ብዛት አንድ ስንኳ የማይታጣው አምላክ ነው [ኢሳ 40፥26/። እግዚአብሔር መልካም ሥራ ይሠራል፤ ከሰማይም ዝናብንና ፍሬን የሚሆንበትን ወራት ይሠጣል |ሐሥ 14፥17/፡፡

1.1.2. በኅሊና ሕግ

በሰው ውስጥ ያለው የኅሊና ሕግ እግዚአብሔር መኖሩን፣ ሕልውናው ያረጋግጣል /ሮሜ 2፥14-15/፡፡

1.2. የእግዚአብሔር ማንነት

እግዚአብሔር መንፈስ ነው። ስለሆነም እግዚአብሔር የሚታይ፣ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ አካል የለውም። እግዚአብሔር ውሱንነት የሌለበት፣ አንዳች የሚሳነው ነገር የሌለ |ሁሉ በሁሉ/ የሆነ ፍፁም አምላክ ነው። ከፍጥረቱ ተለይቶ በራሱ የሚኖር ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ያለው እንደሁም እኔነት (personality) ያለው አምላክ ነው። እግዚአብሔር የሚሰገድለትም በእውነትና በመንፈስ ነው። /ዮሐ 4፥24/።

1.2.1. እግዚአብሔር መንፈስ ነው

እግዚአብሔር መንፈስ እንደመሆኑ የሚዳሰስ፣ የሚታይ ወይም እንደዚህ ባለ ሁኔታ የሚታወቅ አካል የለውም። እግዚአብሔር መልክ፣ ቅርፃዊ አካል (Form and complexim) የለውም /ዘዳ 4፥15-16/። እግዚአብሔር የሚታይ ሕልውና የሌለው፤ እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም /ዮሐ 1፥8/፡፡ እግዚአብሔር የሚሰገድለትም በእውነትና በመንፈስ ነው /ዮሐ 4፥24/።

1.2.2. ውሱንነት የሌለበት ነው

እግዚአብሔር በማንነቱም ሆነ በባሕርያቱ አንዳች ውሱንነት የሌለበትና ይህ ቀረው የማይባል አምላክ ነው። እግዚአብሔር በሥፍራ ሊወሰን አይችልም /1ነገሥት 8፥27/። እግዚአብሔር ሰማይ ዙፋኑ ምድር የእግሩ መረገጫ የሆነ ሰማይና ምድርን ሁሉ የሞላ አምላክ ነው /ኢሳ 66፡1/። እግዚአብሔር ሁሉን የሚችል ከዚህ መለስ ሊባል የማይችል ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሊመረመር የማይችል ነው /ኢዮብ 1፥7-10/።

ከፍጥረቱ ተለይቶ በራሱ የሚኖርና ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ያለው አምላክ ነው። እነዚህ ሁለት እውነታዎች በእግዚአብሔር ዘንድ በስምምነት አሉ፡፡

1.2.3. እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ተለይቶ በራሱ ስለመኖሩ

እግዚአብሔር ከሰው ልጆችና ከፍጥረቱ ሁሉ ተነጥሎ የሚኖር አምላክ ነው። እግዚአብሔር ከፈጠረው ፍጡር ሁሉ የሚበልጥ ከፍ ያለ አምላክ ነው። የእግዚአብሔርን ከፍጥረቱ ተለይቶ መኖርና መለኰታዊ ልቀት በሚመለከት በኢሳይያስ መጽሐፍ ምዕራፍ 55፥8-9 እናያለን። አሳቤ እንደ አሳባችሁ፤ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር።

ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤ ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው

  • እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ የሚቀመጥ አምላክ ነው /ኢሳ 6፥1/፡

  • እግዚአብሔር በቅድስናው ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ነው /ኢሳ 6፥3/፡፡

  • ስለሆነም እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር በአንድ ላይ የሚኖር አምላክ አይደለም ኢሳ 57፡15/፡፡

1.2.4. እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ግንኙነት ያለው ስለመሆኑ

እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ግንኑነት ያለው አምላክ ነው ስንል፡- እግዚአብሔር በተፈጥሮና በሰው እንዲሁም በታሪክ ውስጥ ያለውን ሕልውናና እንቅስቃሴ ማመልከታችን ነው፡፡ ስለሆነም ሰው ከእግዚአብሔር ተሰውሮ በሚስጥር ምንም ዓይነት ነገር ሊያደርግ አለመቻሉን ለመግለጽ ነው፡፡

  • በስውር ብንሸሸግ እርሱ ያየናል፡፡ እግዚአብሔር የቅርብ አምላክ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለም /ኤር 23፥23/፡፡

  • ሰው በስውር ቢሸሸግ እግዚአብሔር ያየዋል ኤር 23፥24/፡፡

  • የእግዚአብሔር መንፈስ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋርና ከእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ይኖራል /ኢሳ 63፡1፣ ሚኪ 3፥8፣ሐጌ 2፥5/፡፡

1.2.5. እግዚአብሔር እኔነት (personality) ያለው አምላክ ነው

“እኔ እኔ ነኝ” “ያለና የሚኖር” በሚል አገላለጽ እግዚአብሔር እርሱ ራሱን ከሌሎች ነጥሎ ሌሎችን ደግሞ ለየራሳቸው ለይቶ ሊያነጋግር መቻሉ በግልጽ ይታያል። እኔነት ያለው በመሆኑ እውቀቱን ስሜቱን ፈቃዱን ሲያሳይና ሲገልጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመልክቶአል።

  • እግዚአብሔር ለሰው እውቀትን ያስተምራል ይገሥጻል ይዘልፋል Iመዝ (94)፥10፡፡

  • እግዚአብሔር የሰዎች ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል /መዝ (94)፥7/፡፡

  • እግዚአብሔር ያዝናል /የሐዘን ስሜቱን ይገልጻል/ /ዘፍ 6፡6/፡፡

                            ትምህርት ሁለት

                        የእግዚአብሔር ባህርያት

በመጽፍ ቅዱስ ውስጥ የእገዚአብሔር ባህርያት በብዙ መንገዶች ተገልጿል። እግዚአብሔር ለሰው የማያጋራቸው /የማያከፍላቸው እና ለሰው የሚያጋራቸው /የሚያካፍላቸው ባህርያት አሉት። እግዚአብሔር ለሰው የማያካፍላቸው ባህርያት ለእግዚአብሔር ብቻ የተለዩ፣ ሰው በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊጋራቸው የማይችሉ ባህርያት ናቸው። ከእነዚህም ባህርያት ውስጥ እግዚአብሔር በሁሉም ሥፍራ መገኘቱ ሁሉን አዋቂ መሆኑ እና ሁሉን ቻይ እንዲሁም የማይለወጥ መሆኑ ከራሱ በስተቀር እግዚአብሔር ለማንም የማያጋራው የማያካፍለው ባህርያት ናቸው።

2.1. እግዚአብሔር የማያጋራቸው የማያካፍላቸው ባህርያት

2.1.1. እግዚአብሔር በሥፍራና በጊዜ ያልተወሰነ ነው

  • ሥፍራ አይወስነውም፤ እግዚአብሔር በሙላት በአንድ ጊዜ በሁሉም ሥፍራ ይገኛል /ዘዳ 4፥39፣ መዝ 139፥7-0፣ ኤር 23፥24/።

  • ጊዜ አይወስነውም፤ ዘለዓለማዊ ነው፤ እግዚአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም /ዘፍ 21፥ 33፣ መዝ (90)፥2፣ 102፥ 25፣ ኢሳ 57፡5/።

2.1.2. እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው

  • እግዚአብሔር ስለማናቸውም ነገር ሙሉ እውቀት አለው /መዝ 139፥5፣ዮሐ 3፥20/።

  • ይህንንም እውቀት እግዚአብሔር ከሌላ ከማንም ከምንም ምንጭ ወይም ኃይል ያገኘው /የተማረው ሳይሆን በዘላለም መለኰታዊ ባህርይው ከእርሱ ዘንደ ያለ እውቀት ነው /ኢሳ 40፥3-4፣ 1ቆሮ 2፥6/።

2.1.3. እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው

  • እግዚአበሔር ሙሉ ኃይልና ችሎታ ያለው ምንም የማይሳነው ምንም የማይታክተው አምላክ ነው።

  • እግዚአብሔር የሌለን ነገር ከምንም መሥራት መፍጠር ይችላል፡፡ ነፋስና ዝናብ ሳይኖር ሸለቆን በውኃ ይሞላል /2ነገሥ 3፥718/።

  • የማይመረመረውን ታላላቅ ነገር የማይቆጠረውንም ተዓምራት ያደርጋል ኢዮብ 9፥10/።

  • እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ማድረግ ከመቻሉም በላይ ሃሳቡን ሊከለክልና ሊያደናቅፍ የሚችል የለም [ኢዮብ 42፥2/።

  • እግዚአብሔር ምንም የሚያቅተው ነገር የለም /ኤር 32፥17/።

2.1.4. እግዚአብሔር የማይለወጥ አምላክ ነው

እግዚአብሔር በባሕርይው ፍፁም የማይለወጥ አምላክ ነው /ዘኁ 23፥19፣ ኢሳ 46፥9-10፣ ሚል 3፥6፣ መዝ 33፥1፣ ያዕ 1፥7/። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች /ዘፍ 6፥6፣ ኢሳ 38፥1-5፣ ዮናስ 3፡10/ ላይ እግዚአብሔር እንደተጸጸተ ይናገራል። ይህ አባባል ሰዎች በሚገባቸው ዓይነት የተጻፈ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ዓላማ እንዲቀየሩ ያለውን ፍላጎት የእነርሱንም መመለስ የሚያሳይ እንጂ እግዚአብሔር ከዘላለም ዕቅዱ መመለሱን የሚያሳይ አይደለም።

  • እግዚአብሔር ሐሰትን ይናገርና ይጸጸት ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም /ዘኁ 23፥19/፡፡

  • የእግዚአብሔር ምክርና ፈቃድ የጸናች ናት አትለወጥም /ኢሳ 46፥9-10/፡፡

  • እግዚአብሔር አይለወጥም ሚል 3፡6/፡፡

2.2. እግዚአብሔር ለሰው የሚያጋራቸው /የሚያካፍላቸው ባህርያት

እግዚአብሔር ለሰው የሚያጋራቸው /የሚያካፍላቸው/ ባሕርያት ቢያንስ በተወሰነ ደረጃና በተወሰነ መጠን በሰው ውስጥ ልናገኛቸው የምንችለው ባሕርያት ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ ለምሳሌ ፍቅር፣ እውነት፣ ቅድስና የመሳሰሉት ናቸው።

2.2.1. እግዚአብሔር ፃድቅ ፈራጅ ነው

እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ፤ ፍፁም ስህተት የሌለበት አምላክ ነው /መዝ 116፥5፣ 145፥7/፡፡ የእግዚአብሔር ፃድቅ ፈራጅነ በኃጥ እርሱን በሚያa ሰዎች መካከል በምድር ላይ በሚሠጠው ፍርድ ይታያል /2ዜና 12፡5-8፣ ነህ 9፥7-8/፡፡ በዘመን መጨረሻ ሰዎችን በማጽደቅና በመኰነን ተግባሩ /ሐሥ 17፥21፣ መዝ 96፥13፣ ሮሜ 2፡8-11/ ሁሉ ጽድቁ ይታያል /መዝ 96፥1፣ ሐሥ 17፥21፣ ሮሜ 2፥8/።

  • እግዚአብሔር ጻድቅ መሐሪና ይቅር ባይ ነው /መዝ (16)፥5/፡፡

  • እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ፤ በሥራው ቸር ነው /መዝ (45)፥7/፡፡

  • እግዚአብሔር በዘመናት የታመነና ቃሉን የሚፈጽም ነው /ነህ 9፡7-8/፡፡

  • እግዚአብሔር በሰው ፊት አያዳላም /ሮሜ 2፥1/፡፡

2.2.2. እግዚአብሔር ፍቅር ነው

እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱና በረከቱ በሰዎች ሕይወት ውስጥ እንዲፈጸም የሚሻ አምላክ ነው /ዮሐ 4፥8፣ ሮሜ 8፥32 ይህንንም አፍቃሪነቱን በልዩ ልዩ መንገድ ገልፆአል። እግዚአብሔር ፍቅሩን ከገለጠባቸው መንገዶች ውስጥ።

  • አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም ቤዛ (ምትክ) እንዲሆን አሳልፎ መስጠቱ /3፡16 ኤፌ 1፡6-7፣ 1ዮሐ 4፥9-10/።

  • የርኅራሄውና የምህረቱ ብዛት /መዝ 103፥8፣ 86፥5፣ ሚኪ 7፥18፣ ኤፌ 2፡4-5/

  • ከፍ ያለው ትዕግሥቱ ጴጥ 3፥20/። ይህ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖህ ዘመን ሰዎች ከእግዚአበሔር ሐሳብና ፈቃድ ወጥተው ሳሉ፤ ለብዙ ጊዜ ታግሷል። አሁንም እግዚአብሔር በዚህ ዘመን በብዙ ይታገሰናል።

  • ልጆቹን መቅጣቱ፡፡ እግዚአብሔር ልጆቹን ሲያጠፉ የሚቀጣ አምላክ መሆኑ፤ ለልጆቹ ያለውን ፍቅር ያሳያል /ዕብ 12፥6-7/።

2.2.3. እግዚአብሔር እውነተኛ አምላክ ነው

እግዚአብሔር በሚናገረው ቃልም ሆነ በሚሠጠው ተስፋ ምንጊዜም እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ይታያል /2ሳሙ 7፥28፣ መዝ 146፥6/። በቃሉ የሚሰጠው መመሪያም ሆነ የተስፋ ቃል አስተማኝና ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚነት ያለው ነው /ዘኁ 23፥9፣ 1ሳሙ 15፥29/።

2.2.4. እግዚአብሔር ቅዱስ ነው

እግዚአብሔር በጽድቅና በንጽህናው ፍፁምነት የሚወዳደረው ማንም ምንም የለም።

  • እግዚአብሔር ከቅድስናው ተካፋዮች እንድንሆን እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፤ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁሉ (ጴጥ 1፥15፣ዘሌ 20፥7-8) በማለት ይመክረናል (ዘሌ 20፥7-8፣ 1ጴጥ 1፥5)።

  •  በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ የለም /መዝ (92)፥5/።

2.2.5. እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ሥልጣን ያለው ነው

የእግዚአብሔር ሥልጣንና ገዢነት ከሁሉ በላይና ተወዳዳሪ የሌለው በመሆኑ፤ ፈቃዱ ሊሻር ወይም ሊለወጥ አይችልም /1ዜና 29፥12፣መዝ 29፡0፣ 83፣ 18፣ 135፡5-6/።