black blue and yellow textile

ነገረ ድኅነት

ክፍል አንድ - ኃጢአት

ክፍል ኹለት - ድኅነት                    

                                                              ክፍል አንድ

                                                                                              ኃጢአት

             1. የኃጢአት ምንነት

      ἁμαρτία (ሀማርቲያ) “ኃጢአት” የሚለው የጽርእ (ግሪክኛ) ቃል በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ ከ391 ጊዜ በላይ የተጠቀሰ ሲኾን፥ በዐዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ ደግሞ ወደ 173 ጊዜ ገደማ በጥቅም ላይ ውሏል። ኃጢአት በእግዚአብሔር ቃል በተገለጸው መሠረት ቅዱሱን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቃወም ወይም ትዕዛዙን በድርጊትና፣ በአስተሳሰብ፣ ወይም በባሕርይ መተላለፍ ማለት ነው። ይህንን በበቂ ኹኔታ ለመእዳት በቅድሚያ የኃጢአትን ምንነት በትክክል መረዳት የሚያስችሉ አራት ነጥቦችን መመልከት ያስፈልጋል።

             1.1. ራስ ገዝ መኾን

      ብዙውን ጊዜ ኃጢአት ተደርገው ከማይቆጠሩ ነገሮች መካከል አንዱ “ራስ ገዝ መኾን” ነው። ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አገዛዝ ስር እንዲኾን፤ ጌታውና ንጉሡ እርሱ ብቻ እንዲኾን ነበር። በሌላ አገላለጽ ሰው ፈቃዱ ወደ ራሱ እንዳይኾን ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ፈቃዱን ለአምላኩ በማስገዛት እንዲኖር የተፈጠረ ነበር። ይህ ፍጥረት በመጀመሪያ ኃጢአት የሠራው እንደ እግዚአብሔር ራስ ገዝ ለመኾን በመፈለጉ ምክንያት ነበር። በዘፍ. 3፥22 ላይ “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤” የሚለው ቃል ሰው ራስ ገዝ ወደ መኾን እንደ ተሸጋገረ የሚያመለክት ነው። በተጨማሪም በዚህ ጉዳይ ስር ሊካተቱ የሚችሉ ነገሮች መካከል አንዱ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራስን መውደድ ነው። ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ከኾኑ ነገሮች መካከል አንዱ፥ የሰው በእግዚአብሔር ግዛትና አገዛዝ ስር መኾን አለመፈለግ እና በራስ ገዝነት ከአስተዳዳሪው ጌታ መለየት ተጠቃሹ ነው።

            1.2. ዓመጽ

       ሐዋርያው ዮሐንስ ግልጽ በኾነ ኹኔታ “ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ ዓመፅን ደግሞ ያደርጋል፥ ኃጢአትም ዓመፅ ነው፤” በማለት ኃጢአት ዓመጽ መኾኑን ያስረዳል (1ዮሐ. 3፥4)። ዓመጽ ማለት ተቃውሞ ማስነሣት ወይም በክፉ ልብ ተነሣሽነት አለመታዘዝን መግለጽ ማለት ነው። በእግዚአብሔር ላይ ልብን ማደንደንና ለመስማት ፈቃደኛ አለመኾን እንዲሁም እልከኝነት ተደርጎም ተገልጿል (ሕዝ. 2፥1-5፤ ዕብ. 3፥7-19)። ሰዎች በኹለት መንገድ አመጸኞች ሊኾኑ ይችላል፤ በመጀመሪያ እግዚአብሔር አድርጉ ያለውን ባለማድረግ (1ሳሙ. 15፥1-23) እና ሌላው ደግሞ እግዚአብሔር አታድርጉ የሚለውን በማድረግ (ሉቃ. 6፥46፤ ያዕ. 4፥17)። ዓመጸኞች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም (1ቆሮ. 6፥9)።

           1.3. ዒላማን መሳት

     ብዙ ጊዜ “ኃጢአት” ለሚለው ቃል በጥቅም ላይ የሚውለው ἁμαρτάνω (ሀማርታኖ) የሚለው የጽርእ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም “ትልምን መሳት” ወይም “ዒላማን መሳት” የሚል ትርጉም የያዘ ነው። እንዲህ ያለው ኃጢአት ከታቀደው ውጪ ግብ አድርጎ በመመላለስ ወይም በመፈጸም የሚመጣ ነው። ለምሳሌ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ... ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ” (ማቴ. 5፥44-45) የሚለውን ትእዛዝ በመጣስ ጥላቻና ክፍ ማድረግ ውስጥ ከተገባ፥ በእግዚአብሔር የተቀመጠውን ዒላማ መሳት ይባላል። ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር ዐሳብ ጋር የሚቃረን በመኾኑ ምክንያት ኃጢአት ይኾናል። አዳምና ሔዋንም እንዳይበሉት የተነገራቸውን ፍሬ በመብላታቸው ወይም ከተቀመጠላቸው ዒላማ ውጪ በመንካታቸው ምክንያት ኃጢአትን ሠርተዋል (ዘፍ. 2-3)። የእግዚአብሔርን መንገድ ትቶ ወደ ገዛ መንገድ ማዘንበል ወይም ወደ ታለመለት ዓላማ አለማቅናት ከእግዚአብሔር ዕቅድ ውጪ መንቀሳቀስ ነውና ኃጢአት ይኾናል።

         1.4. አለማመን

      አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር የተናገረውን አለማመናቸው የኃጢአት ጅማሬ ነበር (ዘፍ. 3፥1-6)። መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ እንደሚናገረውም እግዚአብሔርንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን አለማመን ኃጢአት ነው (ዮሐ. 3፥18፤ 16፥9-10፤ ሮሜ. 14፥23፤ ዕብ. 11፥6)። ሰው የዘላለምን ሕይወት የሚያገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን በኩል በመኾኑ ምክንያት ይህንን እውነት አለመቀበልና መካድ ኃጢአት ነው። እግዚአብሔር ኃጢአትን ለማስወገድ ያዘጋጀውን መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አለመቀበል (አለማመን) እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው። ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ አለመኾንና የእግዚአብሔርን የተሐድሶ ኪዳን መናቅም አመጽ ነው።

          2. የኃጢአት ውጤት

        እንደ አጠቃላይ ኃጢአት በሰው ላይ ያስከተለው ውጤት ሞት ነው። ይህ የሞት ውጤት ደግሞ አካላዊ፣ መንፈሳዊ እና ዘላለማዊ ውጤቶችን የሚያካትት ነው። ሰው ኹሉ ኃጢአትን አለመሥራት ስለማይችል ውጤቱ ለኹሉም የሚደርስ ነው (ሮሜ. 3፥23)።

         2.1. አካላዊ ውጤቱ

በዋናነት የኃጢአት አካላዊ ውጤቱ ሥጋዊ ሞትን ማስከተሉ ነው። በዘፍ. 3፥22 ላይ ሰው “ለዘላለም እንዳይኖር” ይልቁንም ወደ መጣበት መሬት እንዲመለስ እግዚአብሔር ደንግጎበታል (3፥19-20)። ስለዚህ ኃጢአት በሰው ልጅ ላይ ሥጋዊ ሞት እንዲነግሥ ምክንያት ኾኖአል (ኢዮ. 34፥15፤ መክ. 12፥7፤ ማቴ. 10፥28)። ኃጢአት ሥጋዊ ሞትን ብቻ ሳይኾን መከራን፣ በሽታን፣ የተፈጥሮ መዛባትንና የእርስ በእርስ ጥላቻን አስከትሏል። የሰው ልጅ ለኑሮ ተስማሚ ከነበረው ኤደን ገነት የወጣው በኃጢአት ምክንያት ነበር (3፥17-18)። ሔዋን በጸነሰች ጊዜ ጭንቅ እንዲበዛባት፣ በጭንቅ እንድትወልድ፣ እና ፈቃድዋ ወደ ባልዋ እንዲኾን ያደረገው ኃጢአት ነው። ምድር የተረገመችው፣ አዳም በሕይወት ዘመኑ ኹሉ በድካም እንዲመላለስና እንዲሠራ ያስፈረደበት ኃጢአትን በማድረጉ ምክንያት ነበር። እንዲህ ያለው ውጤት ሰው ለኾነ ኹሉ የሚደርስ ሲኾን፥ ሊወገድ የሚችለው በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ብቻ ነው። ስለዚህ ኃጢአት በሰው አካላዊ እንቅስቃሴ ላይ በሽታን አስገብቶአል፤ አካላዊ ሞትንም አስከትሎበታል፤ ከዚህም የሚያመልጥ የለም።

         2.2. መንፈሳዊ ውጤቱ

      ኃጢአት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ጤናማ ኅብረት እንዲቋረጥ ምክንያት ኾኖአል። ነቢዩ ኢሳያስ “ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል፤” በማለት ይናገራል ()። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ ከረከሰ ነገር ጋር ኅብረት አያደርግም። ሰው በኃጢአት በወደቀ ጊዜ የረከሰ ፍጥረት ኾኖአል፤ በዚህም ምክንያት ከቅዱሱ አምላክ ጋር ኅብረት ማድረግ ስለማይችል ከኤደን ገነት ተባሯል። ሰው በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት መንፈሳዊ ሞት ደርሶበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤” በማለት እና “የኃጢአት ደመወዝ ሞት” መኾኑን በመግለጽ ኃጢአት መንፈሳዊ ሞትን እንዳስከተለ ያስረዳል (ኤፌ. 2፥14፥18፤ ሮሜ. 6፥23)።

       ኃጢአት ሰዎችን የእግዚአብሔር ጠላቶች እንዲኾኑ አድርጓቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን” በማለት ሰዎች በኃጢአት ምክንያት የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ ኾኑ ይገልጻል (ቆላ. 1፥21)። ኃጢአት ሰዎችን በባርነት ስር ጥሎአቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተናገረው “ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው፤” (ዮሐ. 8፥34)። በተጨማሪም ኃጢአት ሰዎችን የዲያቢሎስ ባርያዎች እንዲኾኑ አድርጓቸዋል። “በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው፤” (ኤፌ. 2፥2)። ስለዚህ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ኅብረት መጉደልን፣ መንፈሳዊ ሞትን፣ ጠላትነትን እና የኃጢአትና የዲያቢሎስ ባርነትን አስከትሏል።

          2.3. ዘላለማዊ ውጤቱ

      ኃጢአት ከአካላዊና ከመንፈሳዊ አሉታዊ ውጤቱ በተጨማሪ ዘላለማዊ ውጤትን ያስከተለ ነው። ይህም የሰው ልጅ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ተለይቶ በሞት እንዲኖር የሚያደርግ መኾኑ ነው። ሰዎች ሁሉ ከሞት በኋላ በእግዚአብሔር የፍርድ ዙፋን ፊት ይቀርባሉ። በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ባዘጋጀው የመዳኛ መንገድ በክርስቶስ አምነው ባልተገኙት ላይ ዘላለማዊ ፍርድ ይበየናል። ይህ ፍርድ ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየትን እና ዘላለማዊ ሞትን የሚያስከትል ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው። በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ፤” በማለት ዘላለማዊ ሞት መኖሩን ይጠቁማል ()።


                                                         

                                                                                                   ክፍል ኹለት

                                                                                                   ድኅነት

             1. የድኅነት ምንነት

        ድኅነት (ሶቴርያ) የሚለው ቃል በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ሰፊ ትርጉም የያዘ ነው። የኃጢአት ስርየት ከማግኘት ጋር በተያያዘ (ሉቃ. 1፥77)፣ የኢየሱስን አዳኝነት ለማመልከት (ሉቃ. 19፥9፤ ዮሐ. 4፥22፤ ሐዋ. 4፥12፤ )፤ እንደ አጠቃላይ “ከድኅነት” ጋር በተያያዘ (ሐዋ. 13፥26፤ 16፥27፤ ሮሜ. 10፥1፤ 11፥11፤ 2ቆሮ. 6፥2)፣ የመዳንን ወደ ፊታዊነት ለመግለጽ (ሮሜ. 13፥11፤ ፊል. 1፥19፤ 1 ተሰ. 5፥8፤ ዕብ 9፥28፤ 1ጴጥ. 1፥5)፣ ከበሽታ መፈወስን ለማመልከት (ያዕ. 5፥15)፣ ከባርነት ነጻ መውጣትን (ሐዋ. 7፥25)፣ እንዲሁም ከአደጋ መትረፍን ለማስረዳት (ሐዋ. 27፥31፤ ዕብ. 11፥7) በጥቅም ላይ ሲውል ይስተዋላል። በዚህም ምክንያት ድኅነት፥ ኃጢአት በሰዎች ላይ ካስከተላቸው ውጤቶች መትረፍን የሚያመለክት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

             ድኅነት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ፣ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ መኾን፣ ከኃጢአት ባርነትን እና ከዲያቢሎስ አገዛዘ ነጻ መውጣት ማለት ነው። ሰው ከኃጢአት ባርነትና ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ በመውጣት የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሊኾን የሚችለው፥ ስለ ሰዎች ኃጢአት ምትክ በመኾን በመስቀል ላይ በሞተው፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን በተነሣው፣ ወደ ሰማይ ባረገው፣ እንዲሁም ዳግም በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብቻ ነው። በአንዱ በአዳም ኃጢአት ምክንያት በሰው ኹሉ ላይ ሞት እንደመጣ እንዲሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በኩል ለሚያምኑ ኹሉ የዘላለም ሕይወት ተሰጥቷል (ኢሳ. 53፥1-12፤ ዮሐ. 3፥16፤ ሮሜ. 5፥12-20፤ 6፥23፤ ኤፌ. 2፥5፤ ቆላ. 2፥3፤ 1ዮሐ. 1፥2)። ድኅነትን በትክክል ለመረዳት ደግሞ ወደ ድኅነት ሊመሩ የሚችሉ ነገሮችን እና “ድኅነትን” ለይቶ መረዳት ያስፈልጋል።

              መዳን ከእውቀትም ካለመሳሳትም በላይ እንደ ኾነ መረዳት ያስፈልጋል። መዳን ማለት ራስ ገዝ ከኾነ ሕይወት ነጻ በመውጣት እግዚአብሔር ገዝ ወደ ሕይወት መሸጋገር ነው። መዳን ማለት ከዓመጸኝነት በመመለስ ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ነው። መዳን ማለት እግዚአብሔር ያሰበውን እና ያቀደውን በመፈጸው ዒላማውን ማሳካት ነው። እንዲሁም መዳን ማለት እግዚአብሔር ባዘጋጀው የድኅነት መንገድ በማመን እስከ መጨረሻው መጽናት ማለት ነው።

              2. የክርስቶስ የማዳን ሥራ

             የሰው ልጅ ከኃጢአቱ ነጻ ሊወጣ የሚችለው በክርስቶስ የማዳን ሥራ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” (ሐዋ. 4፥12)። ስለዚህ ሰዎች የሚድኑን በክርስቶስ ሥራ በማመን ነው። የክርስቶስ የማዳን ሥራ ደግሞ “ቃል ሥጋ” መኾኑን፣ በመስቀል ላይ መሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱን እና ዳግም ምጽአቱን የሚያካትት ነው።

                  2.1. ትስጉት

          ትስጉት (Incarnation) የሚለው ቃል አምላክ ሰው የኾነበትን ወይም “ቃል ሥጋ” የኾነበትን ምስጢር ለመግለጽ በጥቅም ላይ ይውላል (ዮሐ. 1፥14)። ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው (ቈላ. 2፥9፤ 1ጢሞ. 3፥16)። ከእግዚአብሔር ጋር የተካከለ ኾኖ ሳለ ራሱን ለመታዘዝ አሳልፎ በመስጠት የባሪያን መልክ የያዘ ነው (ፊል. 2፥6-8)። ምንም እንኳ የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ዘላለማዊ ቢኾንም፥ በክርስቶስ በኩል የተፈጸመው የማዳን ሥራ የሚጀምረም ግን “ቃል ሥጋ” በኾነበት ወቅት ነው። የአምላክ ሰው መኾን የእቅዱ ፍጻሜ መጀመሪያ ነበር። አምላክ ሰው መኾን ያስፈለገበት ምክንያት፥ የሰው ልጆች ከኃጢአታቸው የተነሣ በዲያቢሎስ አገዛዝ ስር ወድቀው ስለ ነበር ነው። በተጨማሪም በሞት ፍርሃት ባርነት ታስረው ስለ ነበር ነው። ስለዚህም በሞት ፍርሃት የታሰሩትን ነጻ ለማውጣት፥ በመጀመሪያ “ቃል ሥጋ” ይኾን ዘንድ እና በሥጋና በደም ወንድሞቹን ይመስል ዘንድ አስፈልጎታል (ዕብ. 2፥14-15። ይህም የሰውን ኃጢአት ለማስወገድ ሰውን ወክሎ ቤዛ (ምትክ) የሚኾን ንጹሕ መሥዋዕት ያስፈልግ እንደ ነበር ያስረዳል። ክርስቶስም የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ ነውር አልባ የእግዚአብሔር በግ በመኾን ራሱን ቤዛ አድርጎ ለዓለሙ ሰጠ (ዮሐ. 1፥29፤)።

                 2.2. መከራውና የመስቀል ላይ ሞቱ

             ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ሆኖ ወደ ዓለም በመምጣት፥ በመስቀል ላይ መሞቱና መነሣቱ ለአማኞች ያስገኘው ውጤት ዘርፈ ብዙ ነው። ከእነዚህ መካከል ቤዛ መኾኑ፣ ሰውን መዋጀቱ፣ ኃጢአትን ማስተስረይ መቻሉ፣ የእግዚአብሔር ቁጣ መቀበሉ እና ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቁ በዋናነት የሚጠቀሱት ናቸው።

           የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞቱ ለሰዎች ቤዛ (ምትክ) መኾኑን የሚያስረዳ ነው። አንዳች ኃጢአት ያልተገኘበት ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞች በሚውሉበት መስቀል ላይ መዋሉ በራሱ ለሰው ልጆች ቤዛ መኾኑን የሚያመለክት ነው። የመስቀል ላይ ሞት እንደ በርባን ላሉ አመጸኞች እና በበደላቸው ምክንያት ቅጣት ለሚገባቸው የተዘጋጀ ፍርድ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ አመጸኞችን እና በደለኞችን ከሞት ቅጣት ያድናቸው ዘንድ ያለ በደሉ ምትክ ኾኖ በመስቀል ላይ ዋለ። ኃጢአትን ያልሠራው ኢየሱስ በሰው ምትክ በመስቀል ላይ እንዲሞት በእግዚአብሔር ተፈርዶበት የሰውን ቅጣት ተቀበለ (ኢሳ. 53፥1-12፤ ሮሜ. 3፥24፣ 5፥6-8፣ 6፥23)።

           ሌላው ደግሞ የመስቀል ላይ ሞቱ መዋጀትን ያስገኘልን ነው። ቤዛ መኾን ማለት በፈንታው ምትክ መኾን ማለት ሲኾን፥ መዋጀት ማለት ግን የራስ ማድረግ ወይም በዋጋ መግዛት ማለት ነው። መዋጀት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አንድ የተሸጠን ባሪያ አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል ነጻ በማውጣት የራስ ማድረግን ለማመልከት ነው፡፡ የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሥራ፥ ሞት የተገባውን ሰውን የደም ዋጋ በመክፈል እንደ ዋጀው የሚያመለክት ነው። ሰው ሁሉ በኃጢአት ቀንበር ስር የወደቀ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ለኃጢአት ዋጋ ይኾን ዘንድ ራሱን በመስቀል ላይ በማቅረብ እና ደሙን በማፍሰስ ለሚያምኑበት ሁሉ የሚኾን ነጻነትን አስገኝቶአል። ስለዚህ በመስቀሉ ሥራ በኩል በተደረገ መዋጀት በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምኑ ሁሉ በዋጋ የተገዙ ከባርነት ቀንበርም ነጻ የወጡ ናቸው (ሮሜ. 3፥24፣ 8፥23፤ 1ቆሮ. 1፥30፣ 5፥20፤ 7፥23፤ 1ጴጥ. 1፥18-19)።

         የኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ቤዛ የመኾን እና ሰዎችን የመዋጀት ፋይዳው፥ የሰዎችን ኃጢአት ለማስተስረይ ነው። ሰዎች ከኃጢአታቸው ለመንጻት መሥዋዕት ማቅረብ ያስፈልጋቸዋል (ዕብ. 9፥9-10)። ደም ሳይፈስ ሥርየት ወይም የኃጢአት ይቅርታ ስለ ሌለ፥ ኃጢአቱ እንዲሰረይለት የሚወድ ሁሉ የፍየል፣ የኮርማ፣ የበግ፣ የዋኖስ ወይም የተለያዩ የቁርባን መሥዋዕቶችን ሊያቀርብ ያስፈልገው ነበር (ዘሌ. 16)። ይኹን እንዲ የፍየሎችና የኮርማዎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ እና ሰዎችን ማስተስረይ አይችሉም ነበር (ዕብ. 10፥1-4)። ከዚህም የተነሳ መሥዋዕት አቅራቢዎቹ በሕሊና ፍጹማን ሊኾኑ አልቻሉም ነበር። ስለዚህ ለኃጢአት ማስተስረያ የሚኾን ሌላ ነውር የሌለው መሥዋዕት ይቀርብ ዘንድ ስላስፈለገ፥ ክርስቶስ የሰዎችን ኃጢአት የሚያስተስርይ ነውር የሌለበትን መሥዋዕት ኾነ። ደሙን በኩል የሚገኝ የኃጢአት ይቅርታንም አስገኘ (ዕብ. 9፥12-1፤ ሮሜ. 3፥25፤ 1ዩሐ. 1፥7)።

        በተጨማሪም የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት፣ የቤዛነቱ እና የዋጆው ሌላኛው ውጤት፥ የእግዚአብሔርን ቁጣ ማብረድ ነው። እግዚአብሔር በኃጢዓት ምክንያት ሰውን ኹሉ ተቆጥቶ ነበር። ይህ ቁጣ ሊመለስ የቻለው በመስቀል ላይ በፈሰሰውና እግዚአብሔርን ደስ ባሰኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በኩል ነው። እግዚአብሔር የሰውን ኃጢዓት ይቅር ለማለት ያረካው የልጁ ደም ብቻ ነው። ስለዚህ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዲድኑ የመስቀሉ ሥራ ምክንያት ኾነ (ሮሜ. 3፥24-25፤ 1ዩሐ. 2፥2)። በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ እግዚአብሔር ይቅር ስላላቸው ደግሞ ማንም ሊፈርድባቸው አይችልም (ሮሜ. 8፥33-34)።

        በመጨረሻም የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እርቀ ሰላም የተከናወነበት ነው። ሰው ኹሉ በእግዚአብሔር ላይ በማመጹ ምክንያት የእግዚአብሔር ጠላት ኾኖ ነበር (ቆላ. 1፥21)። ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተቋረጠውን ቤተሰባዊ ኀብረት ለማደስ በመስቀል ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። መካከለኛ በመሆንም ደግሞ የተቋረጠውን ቤተሰባዊ ኀብረት አደሰ (ሮሜ. 5፥10፤ 2ቆሮ. 5፥18-20)። በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ያስገኘው ከእግዚአብሔር ጋር የተደረ እርቅን ብቻ ሳይኾን፥ ከሰዎች እና ከራስ ጋር የተደረገን ጥል በማፍረስ እርቅን አስገኝቶአል።

           2.3. ትንሣኤው

          የክርስቶስ ከሙታን መነሣት በሰዎች ድነት ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ባይነሣ ኖሮ የሰው ልጅ የመዳን ተስፋ አይኖረውም ነበር። ስለ ኃጢአተኞች ራሱን ቤዛ አድርጎ የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሥቶአል። ይህም ምስክርነት በመላእክት፣ በሐዋርያት እና በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ የጸና ነው። መልአኩ፥ “እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ፤” በማለት መስክሮለታል (ማቴ.28፥6)። ሐዋርያቱም፥ “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤” በማለት ያዩትን መስክረዋል (ሐዋ. 2፥32)። ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስም፥ “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ፤” በማለት ትንሣኤውን ለፍጥረት አብስሮአል (ራዕ. 1፥18)።

የክርስቶስ ትንሣኤ ለዘላለም ድነት ዋስትና የሰጠና ለእምነታችንም ማረጋገጫ የኾነ ነው። ኢየሱስም ክርስቶስ እንደ ተናገረው “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤” በማለት የዘላለም የሕይወት ዋስትና ሰጥቶናል (ዮሐ. 11፥25)። እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ፤” (1ቆሮ.15፥17) በማለት እንደ ገለጸው፥ ክርስቶስ ከሙታን ካልተነሣ እምነታችን ርግጠኛ መኾን አይችልም። ነገር ግን “ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል፤” (1ቆሮ. 15፥20)። ስለዚህ የእምነታችን ርግጠኝነት በዚህ ተረጋግጦአል። እኛም እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሳው በመመስከር መዳናችንን እናውጃለን (ሮሜ. 10፥9)።

ሌላው የክርስቶስ ትንሣኤ ይገዛን ከነበረው ሞትና ከሞት ፍርሃት ነጻ አውጥቶናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ ፊት እንዳይሞት ሞትም ወደ ፊት እንዳይገዛው እናውቃለንና፤” በማለት የክርስቶስ ትንሣኤ ሞት እንዳይገዛ እንዳደረገ አስረድቶአል (ሮሜ. 6፥9)። በተጨማሪም ክርስቶስ በመነሣቱና እኛ ከእርሱ ጋር በመነሣታችን ምክንያት የዕዳ ጽሕፈት ተወግዶልናል (ቈላ. 2፥13-15)። ስለዚህ የክርስቶስ ከሙታን መነሣት በሰው ድነት ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው እንረዳለን።

               2.4. ዕርገቱ

           ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ በምድር ላይ ወደ አርባ ቀናት ገደማ ተመላልሶአል። ከዚያም በኋላ ሐዋርያቱ “እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው” (ሐዋ.1፥9)። የክርስቶስ ዕርገት በሰዎች ድነት ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። የክርስቶስ ዕርገት ሊቀ ካህናትነቱን ያረጋገጠ እና ቀጣይነት ያለውን አግልግሎትንም የገለጠ ነው። እንደሚታወቀው በብሉይ ኪዳን አንድ ሊቀ ካህናት መሥዋዕቱን በአደባባይ ላይ ካቀረበ በኋላ ደሙን የሚያቀርበው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ነበር። ይህንን ሥርዓት በስርየት ቀን በዓመት አንድ ጊዜ ለዘወትር ሊያደርገው ያስፈልግ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሥርዓት በመሻር አንዴ ለሁሌ የኾነ መሥዋዕት አድርጎ ራሱን በመስቀል ካቀረበ በኋላ በደሙ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባ ዘንድ ያስፈልገው ነበር። ለዚህም ነው በእጅ ወዳልተሠራችው ወደ ሰማያዊቱ ቅድስት በደሙ በኩል የገባው። ስለዚህ ክርስቶስ በማረጉ ምክንያት በሰማያዊቱ ቅድስት ውስጥ ደሙን ይዞ እንዲገባ አድርጎታል (ዕብ.9 እና 10)።

           ሌላው የክርስቶስ ዕርገት ያስገኘው ፋይዳ ደግሞ አሁንም ድረስ በአብ ፊት ስለ እኛ እንዲታይ አድርጎታል። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራችው ቅድስት (ቅድስተ ቅዱሳን) አልገባም። ይልቅ “ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ” እንጂ (ዕብ.9፥24)። ይህ ስለ እኛ መታየት ደግሞ ከምልጃው ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ቀደሙት ሊቃነ ካህናት ሞት ስላላስቀረው ዘወትር ስለ ሰዎች ይማልድ ዘንድ በሕይወት ይኖራል (ሮሜ. 8፥34፤ ዕብ. 7፥25)። በተለይም ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ. 8፥34 ላይ የሞተው፣ ከሙታን የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው እና ስለ እኛ የሚማልደው በማለት በቅደም ተከተል ማስቀመጡ፥ የክርስቶስ ዕርገት ወይም በአብ ቀኝ መቀመጡ በቀጣይነት ለሚፈጽመው የምልጃ አገልግሎቱ አስፈላጊ እንደ ነበር የሚያመለክት ነው።

          2.5. ዳግም ምጽአቱ

       ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽና በታላቅ ክብር፤ በመላዕክቱ ታጅቦ ዳግመኛ ወደ ምድር ይመጣል (1ተሰ. 5፥2፤ ራዕ. 6፥15፤ ማቴ. 24፥30፤ ማር. 8፥38)። የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በሰዎች ዘላለማዊ ድነት ውስጥ ፋይዳው የጎላ ነው። ይህም በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ከእርሱ ጋር ለዘላለም ወደ መኖር የሚሸጋገሩበት ነው (1ተሰ. 4፥17)። እንዲሁም በዳግም ምጽአቱ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ፤” (ራዕ. 21፥4)።

         3. የድኅነት ሂደት

            3.1. ንስሐ

      ድኅነት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በማወቅ የሚገኝ አይደለም። ነገር ግን ለተረዱት እውነት ምላሽ በመስጠት የሚገኝ ነው። ሰዎች ለተረዱት እውነት ምላሽ የሚሰጡት ደግሞ በንስሐ በኩል ነው። ድነት ከበሽታ መዳን፣ ከሞት መዳን፣ ከጥፋት ወይም ከአደጋ መዳን የሚሉ ትርጉሞችን የያዘ ነው። የሰው ልጅ ደግሞ በገዛ ኃጢአቱ በሽተኝነትን፣ ሞትን፣ ጥፋትንና አደጋን በራሱም በሌሎችም ላይ አስከትሎአል። ስለዚህ ሰው መዳንን ቢወድድ አስቀድሞ ይህን ጥፋተኝነቱን መረዳትና በበደለው በእግዚአብሔር ፊት በንስሐ መቅረብ ይኖርበታል። ምንም እንኳን ድነት ሙሉ በሙሉ የተዘጋጀውና ሥራውም የተሠራው በእግዚአብሔር ቢኾንም፥ የሰውን ምላሽ የሚፈልግ መኾኑ መዘንጋት የለበትም። እግዚአብሔር ሰዎች እንዲድኑበት አንድያ ልጁን አሳልፎ ሰጥቶአል (ዮሐ. 3፥16)፤ ሰዎች ደግሞ ይህንን ስጦታ በእምነት ሊቀበሉ ያስፈልጋል። ንስሐ ደግሞ እግዚአብሔር ላዘጋጀው ድነት የሰው ምልሽ የሚገለጥበት ነው (ማቴ። 3፥2፤ ማር. 1፥15፤ ሉቃ. 13፥3 ሐዋ. 3፥19)።

            3.2. ጽድቅ/ justification

           ጽድቅ የሚገኘው በእምነት በኩል ነው (ሮሜ. 3፥28፤ ገላ. 2፥16፤ ኤፌ. 2፥8-9)። ሰው ደግሞ እግዚብሔር ላዘጋጀው ድነት ምላሽ ሲሰጥ፥ ወይም በንስሐ በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን ይጸድቃል። የሚያጸድቀው ደግሞ እግዚአብሔር ነው (1ቆሮ. 6፥11)። እግዚአብሔር የሚያጸድቀው ደግሞ የእርሱ ሕዝቦች መኾናችንን ነው። ሰው በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ፊት ከቀረበና በክርስቶስ ካመነ በኋላ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይጨመራል። በዚያን ጊዜ ከጻድቃን ጋር በመቆጠር የእግዚአብሔር ሕዝብ ይባላል። በሌላ አገላለጽ ጽድቅ ማለት ከጨለማው አገዛዝ መላቀቅ፣ ቀድሞ ከነበረ በደልና ኩነኔ ነጻ መውጣት እንዲሁም ከኃጢአት ቅጣት በመትረፍ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መጨመር ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ሰው “ጸድቂያለው” ሲል “ተፈርዶብኝ የነበረው የኃጢአት ቅጣት በክርስቶስ ሥራ ተወግዶልኝ ነጻ ወጥቻለሁ” እያለ ነው።

ይህንን ለመረዳት “ጽድቅ” ማለት “ከመዳን” ጋር ተመሳሳይ መኾኑን በመረዳት አፈላጊ ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደ ተሞከረው መዳን ማለት ከኃጢአት ቅጣት መትረፍ ማለት ነው። ከኃጢአት ቅጣት ያተረፈን ደግሞ እግዚአብሔር ነው። ጽድቅም በተመሳሳይ መልኩ ከኃጢአት ቅጣት መትረፍ ማለት ነው። ሰዎች በበደላችን እና በኃጢአታችን ምክንያት ይገባን ከነበረው የኃጢአት ቅጣት በክርስቶስ የመስቀል ሥራ በማመናችን ድነናል ወይም አምልጠናል። ስለዚህ አማኞች ድነናል ስንል ጸድቀናል እያልን ነው፤ ጸድቀናልም ስንል ድነናል እያልን ነው። እዚህ ጋር ልብ ማለት የሚያስፈልገው ግን የዳንነው ከተፈረደብን ሞትና ይገባን ከነበረው የኃጢአት ቅጣት መኾኑን ነው።

          3.3. ቅድስና/ sanctification

        መቀደስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተፈጸመውን ድነት በእምነት ከተቀበልን በኋላ በቀጣይነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና እገዛ በአገኘነው ዐዲስ ሕይወት እየተወረስን፣ በግብረ-ገባዊ ኑሮአችን እግዚአብሔርን እየመሰልን፣ እና በሂደት ድነታችን ፍጻሜ የሚያገኝበት የማይቋረጥ የሕይወት ለውጥ ነው። “መቀደስ” ማለት “መለየት” ማለት ነው። ቅድስና ከኃጢዓት፣ ከርኩሰትና ካልተገባ ሕይወት በሂደት በመለየት ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዓላማ ብቻ መኖርን የሚያመለክት ነው። ስንቀደስ ከዓለም (ኃጢዓት) የምንለይ፥ ነገር ግን በዓለም የምንኖር የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንኾናለን (ዘሌ. 20፥26፤ 1ጴጥ. 1፥15-16)። የተፈጠርነው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ነው (ዘፍ. 1፥27)፤ በመሆኑም እግዚአብሔር ይህ መልክ በሕዝቦቹ ተገልጦ እንዲታይ ይፈልጋል (ኤፌ. 4፥24፤ ቲቶ. 2፥14)። የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ በህይወታችን የሚገለጠው ደግሞ በውስጣችን በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታደስ ነው (2ተሰ. 2፥13)። ይህ የመታደስና እግዚአብሔር እየመሰለ የመኖር ሂደት “ቅድስና” ይባላል። ስለዚህ ቅድስና ለእግዚአብሔር መንፈስ በመታዘዝ፣ ከኃጢአት በመራቅ እና እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ማደግን ያካትታል።

      እንደ ጽድቅ ሁሉ ቅድስናም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው (1ቆሮ. 6፥11)። ይህ ማለት ደግሞ ሰዎች ሊቀደሱ የሚችሉት በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በማመናቸው ብቻ እንደ ኾነ ያስረዳል። ይኹን እንጂ ቅድስና ከኃጢአት ቅጣት የምንተርፍበት ሳይኾን፥ ከኃጢአት ኃይል የምንድንበት ነው። በጽድቅ በኩል ከኃጢአት ቅጣት የዳንን ሲኾን፥ በቅድስና በኩል ደግሞ ከኃጢአት ኃይል እንድናለን። ይህም ቅድስናን የዘወትር እንዲኾን ያደርገዋል፤ ወይም እየዳንን ያለን መኾናችንን ያመለክታል። እግዚአብሔር በሠራው ፍጹም ሥራ በኩል የራሱ ሕዝቦች አድርጎናል። ከእርሱ ጋር ለመኖርና እስከ መጨረሻው ለመጽናት ደግሞ ከኃጢአት ኃይል እያመለጥን በቅድስና ልንኖር ያስፈልጋል። ይህም የድነትን ቀጣያዊነት የሚያስረዳ ነው። ኃጢአት እስካለ ድረስ የኃጢአት ኃይል ይሠራል፤ ከዚህ ኃይል ማምለጥ የሚቻለው ደግሞ ለእግዚአብሔር በመለየት (በመቀደስ) ነው። ቅድስና ደግሞ የአንድ ጊዜ ድርጊት ሳይኾን፥ በየዕለት በሚደረግ ውሳኔ ከኃጢአት ኃይል እየዳንን የምንኖርበት ነው ።

       ቅድስና በየዕለቱ ከኃጢአት እየተለየን የባሕርይ ለውጥ የምናመጣበት ሂደትም ነው። ኢየሱስ በየዕለቱ ኃጢአትን እያስወገድን (ቆላ. 3፥5-9) መልካም እድናደርግ ይፈልጋል (ቆላ. 3፥12-14፤ ቲቶ. 2፥14)። ይህ ሂደት አሁን የተቀደሰ ሕይወት እንዲኖረን ያስችለናል (1ተሰ. 5፥23፤ 1ጴጥ. 1፥14-16)። በእግዚአብሔር ቃል በመታደስ (ኤፌ. 5፥26፤ 2ጢሞ. 3፥16፤ ዩሐ. 17፥17)፣ በመንፈስ-ቅዱስ አሠራር (2ተሰ. 2፥13)፣ በእግዚአብሔር አባታዊ ቅጣት (ዕብ. 12፥10)፣ እና በመከራ ውስጥ በማለፍ (1ጴጥ. 4፥1-2) የቅድስናን ሕይወት እንለማመዳለን። በዚህ ውስጥ የአማኙ ድርሻ የቅድስናን ሕይወት መፈለግና ማድረግ ይኾናል (ዕብ. 12፥14)። ይህም አካልን (ብልቶቹን) ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ (ሮሜ. 6፥12-13፤ 12፥1) እና ለቃሉ በመታዘዝ (ዩሐ. 14፥23፤ 2ዮሐ. 6-9) የሚተገበር ነው።

         ከአሮጌው ሰው የሕይወት ሥርዓት በሂደት እየተለየን እንጓዛለን (ገላ. 5፥24፤ ሮሜ. 6፥6)፤ በዐዲሱ ሰው የሕይወት ሥርዓት ደግሞ በሂደት እንወረሳለን (2ቆሮ. 5፥7፤ ቆላ. 3፥10)። ቅድስናችን በምድራዊ ሕይወታችን ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ አይችልም። ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ወይም እኛ በአካላዊ ሞት ወደ ጌታ ስንሄድ ቅድስናችን ተፈጽሞ ፍጹማን እንሆናለን (ኤፌ. 5፥27፤ ዕብ. 12፥23፤ 1ዮሐ. 3፥2፤ ይሁዳ 24)። አሁን ኃጢአት የለብኝም (ቅዱስ) ነኝ የሚል ሐሰተኛ ነው (1ዩሐ. 1፥8)። አሁን የለበስነው አካል ገና ያልተዋጀ (ያልከበረ) በመሆኑ እንዲሁም የምንኖርበት ዓለም በኃጢአት ምክንያት የተረገመች በመኾንዋ፥ ኃጢአትን አሸንፈን ፍጹም (ቅዱስ) ልንሆን አንችልም (ሮሜ. 8፥18-25)። የኃጢአት ኃይል እንዳይሰለጥንብን ግን በቅድስና ልንመላለስ ያስፈልጋል።

          ዳግም ልደት ያገኘ አማኝ፤ ከቀደመው ኃጢአቱ በክርስቶስ ደም የታጠበ፣ በመንፈስ ቅዱስም ዳግም የተወለደ፣ እንዲሁም ክርስቶስ በከፈለው ዋጋ በኃጢአት ላይ ድል ያገኘና ኃጢአትን ላለማድረግ በልቡ የወሰነ ሰው ነው። ዳግም የተወለደ ሰው ወይም ክርስቲያን ለኃጢአት ሞቶ ለጽድቅ ለመኖር በመነሳቱ ኃጢአትን የመጥላትና ከኃጢአት የመራቅ ዝንባሌ አለው። ኃጢአትን ማድረግ ዳግም ልደት ያገኘ ሰው ባህርይ አይደለም። የኃጢአት ሃሳብ እንኳን ቢመጣ ፈጥኖ ይቃወማል እንጂ፥ ተጥለፍልፎ አይወድቅም። ሆኖም ግን ይህ ዳግም የተወለደ ክርስቲያን የሚኖረው በዓለም በመኾኑ፥ በዓለምና በሥጋው ምኞት እየተሳበ እንዲሁም በሰይጣን እየተታለለና እየተሳሳተ ኃጢአት ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ሁል ጊዜ በንስሐ ሕይወቱን እያደሰ ከክርስቶስ ጋር ይኖራል (1ቆሮ. 6፥18፤ ዕብ 3፥13፤ 12፥6፤ 1ዮሐ. 1፥8-10፤)። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲገለጽ፥ አንድ ሰው ያገኘውን መዳን ተግቶ በቅድስና መጠበቅ ይገባዋል። ይኸውም ከኃጢአት፣ ከዚህ ዓለም ርኩሰት፣ ከስንፍናና ከዲያብሎስ ሽንገላ ሁሉ ራስን መለየት (መቀደስ) እና እስከ መጨረሻው መጽናት ነው (1ጢሞ. 6፥12-16፤ 2ጢሞ. 2፥11-13፤ ዕብ. 10፥36)።

             3.4. ክብር

          ፍጻሜ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመጣ አሁን የለበስነው አካላችን ተለውጦ የማይበሰብሰውን የትንሣኤ አካል እንለብሳለን። በዚህ ጊዜ ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ስለሚወገድ ፍጹማን እንኾናለን (1ቆሮ 15፡25-27)። ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ በትንሳኤው አካል በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ፥ አማኞችም የክርስቶስን የሚመስል አካል በመልበስ ከክርስቶስ ጋር ይከብራሉ። የአማኞች ክብር በአጠቃላይ የእግዚአብሔርን ዘላለም ወደ መለማመድ የሚደርሱበት የመጨረሻው ፍጻሜአቸው ይኾናል። የዐዲስ ኪዳን መጽሓፍት የአማኞችን የወደፊት ክብር በብዙ አቅጣጫ ያስረዳሉ (ማቴ. 25፥1-46፤ ሮሜ. 8፥18-23)። አማኞች በመጨረሻ በመንፈስ ቅዱስ ርስታቸውን ይወርሳሉ (ኤፌ. 1፥13-14፤ 1ጴጥ. 1፥3-5)። በክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ከአማኞች መክበር ጋር የፍጥረት መታደስ ይደረጋል።ምክንያቱም ፍጥረት በሰው ኃጢኣት ምክንያት ስለተረገመ ሰው ዐዲስ ኾኖ ሲለወጥ ፍጥረትም ይለወጣል። ፍጥረት አሁን በተፈጠረበት ክብር ስለማይኖር አሁን በምጥ ውስጥ ይገኛል ።

        ስለዚህ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚከናወነው የሰው ልጆች “መክበር” ዘላለማዊ ድነትን የሚያመለክት ነው። ይህም ማለት ወደ ፊት እንደምንድን የሚያመለክት ነው። በመጽደቅ በኩል ከኃጢአት ቅጣት ድነናል፤ በቅድስና በኩል ከኃጢአት ኃይል እየዳንን ነው፤ በመክበር በኩል ደግሞ ከኃጢአት ከራሱ እንድናለን። የአማኞች ክብር የሚፈጸመው ኃጢአት ወደማይኖርበት የእግዚአብሔር ከተማ በመግባት ነው። አማኞች “ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁ” (ዕብ. 9፥28) እንደ ተባለው፥ ወደ ፊት ሙላቱን የሚያገኘውን ድነታቸውን የሚፈጽመውን ጌታ የሚጠባበቁ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስም “ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና” እንዳለው ሙላቱን የሚያገኝ ድነትን እንጠብቃለን። እንዲሁም “የመዳንንም ተስፋ” ተስፋ የምናደርግም ነን (1 ተሰ. 5፥8)። በተጨማሪም “በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን” በእምነት የምንጠበቅም ነን (1ጴጥ. 1፥5)። እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት የድነትን ወደፊታዊነት ነው። ስለዚህ የአማኞች ክብር ማለት ዘላለማዊ ድነትን በመቀዳጀትና ኃጢአት የማይኖርበት መንግሥት ውስጥ በመግባት፥ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም መኖር መጀመር ማለት ነው።

            እንደ አጠቃላይ ጽድቅ፣ ቅድስና እና ክብር ማለት፥ ድነናል፣ እየዳንን ነው፣ እንዲሁም እንድንለን እንደ ማለት ነው። ከዚህ በመነሣት ጸድቀናል ስንል ድነናል እያልን ሲኾን፥ የዳንነው ደግሞ ከኃጢአት ቅጣት ነው። ተቀድሰናል/እየተቀደስን ነው ስንል እየዳንን ነው ማለት ሲኾን፥ እየዳንን ያለነው ደግሞ ከኃጢአት ኃይል ነው። በተጨማሪም ከብረናል/እንከብራለን ስንል እንድናለን እያልን ሲኾን፥ የምንድነው ደግሞ ከራሱ ከኃጢአት ነው። ጸጋው በእምነት ስላዳነን እንመካለን (ኤፌ. 2፥8)፤ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለኾነ በቅድስና እንኖራለን (1ጴጥ. 1፥15-16)፤ ክብር ስለሚጠብቀን ሐሴት እናደርጋለን (1ጴጥ. 1፥3-5)።

             4. ከድኅነትን የሚያጎድሉ ነገሮች

        ሰው ሊድን የሚችለው በእምነት ነው፤ ድነቱን ሊያጣ የሚችለውም ከእምነት በመጉደል ነው። የዕብራውያን መልእክት ጸሓፊ “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤” በማለት የማካድን አስከፊነት ይናገራል። እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ስለ ኾነ፥ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችል ልጁን ሰጥቶአል (ዮሐ. 3፥16)። መዳንን የሚያገኙትም እንዲድኑ አስቀድመው የተወሰኑ ሰዎች ሳይኾኑ፥ የተቀበሉት ሁሉ ናቸው (ዮሐ. 1፥12)። ነገር ግን በክርስቶስ ካመኑ በኋላ፣ የሕይወታቸው አዳኝና ጌታ አድርገው ከተቀበሉት በኋላ እንዲሁም ሥጋና ደሙን ከወሰዱ በኋላ ወደውና ፈቅደው ቢክዱት በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ እድል ፈንታ የላቸውም።

         ሐዋርያው ጴጥሮስ “በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል፤” (2ጴጥ. 2፥20) በማለት ተናግሮአል። ይህም ከዓለም በማምለጥ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከገቡ በኋላ በዓለም ምኞት ተጥለፍልፈው ቢወድቁ፥ ከመዳናቸው በፊት ከነበረው ኑሮአቸው ይልቅ ይህኛው የከፋ እንደሚኾንባቸው የሚያስረዳ ነው።

መካድ በኹለት ሊከፈል ይችላል። የመጀመሪያው በውሳኔ “ከዛሬ ጀምሮ ኢየሱስ ጌታ ነው ብዬ አላምንም፤” በማለት መካድን ማወጅ ይቻላል። ብዙውን ጊዜ እንዲ ያለውን ክህደት የሚፈጽሙት፥ ወደ ሌላ ቤተ እምነት የሚገቡ እና ምናልባትም አምላክ የለም ወደሚል እምነት የሚንሸራተቱ ሰዎች ናቸው። እንዲህ ወዳለ ክህደት የሚገቡበት ምክንያት ደግሞ የተሻለ መረዳት ያገኙ እየመሰላቸው፣ በጊዜያዊ ጥቅም በመያዝ፣ ወይም በሰዎች ገፋፊነት ሊኾን ይችላል። ኹለተኛው ደግሞ በሕይወት ምልልስ መካድን መግለጥ ይቻላል። እንዲህ ያለው ክህደት ብዙ ጊዜ ለሰዎች የተገለተ አይደለም። ምናልባትም እንዲህ ባለው ልምምድ ውስጥ ያለው አካል፥ ከቤተ ክርስቲያን የማይቀር፣ የሚጸልይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያነብ እና መዝሙር በመዘመር የሚታወቅ ሊኾን ይችላል። ነገር ግን እውነቱ ሲገለጥ፥ በሕይወቱ ላይ ንጉሥና ጌታ አድርጎ ሹሞት የነበረውን ጌታን በመተው የተለያየ ነገር ጌታ አድርጎ የሾመ ሰው ነው። ለምሳሌ በኃጢአት ባርነት ውስጥ በመኾን ኢየሱስ ጌታ ሊኾን አይችል። ወይም በኃጢአት ጸንቶ መኖርና መዳን አንድ ላይ አይሄዱም። አንዳንድ ሰዎች በትክክል ከጌታ ጋር ጉዞ ጀምረው የመዳንን እወቀት ከቀመሱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በመጥለፍለፍ የኃጢአት ባርያ ይኾናሉ። እንዲ አይነት ልምምድና ባርነት ውስጥ የወደቁ ሰዎች፥ በአደባባይ ባያውጁትም እንኳ ከክርስቶስ ሕይወት የጎደሉ ናቸው።

      እንዲህ ካለው ልምምድ እንድንተርፍ የሚያደርገን በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ ዕለት ዕለት በቅድስና መመላለስ ነው። ቅድስና ማለት መለየት ማለት ነው፤ መለየት የሚያስፈልገው ደግሞ እግዚአብሔርን ከማያከብር ነገር ሁሉ ነው። ክርስቲያን በኃጢአት ጸንቶ መኖር አይችልም። ምንም እንኳን በኃጢአት ሊወድቅ ወይም ኃጢአት ሊሠራ ቢችልም፥ የክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ሊያነጻን የታመነ ስለ ኾነ (1ዮሐ. 1፥7) በኃጢአት ባርነት ስር አይገኝም። ምክንያቱም የክርስቶስ ደግም ኃጢአት የማድረጊያ ዋስትና ሳይኾን፥ ለወደቁት መነሻ ለተነሡት ደግሞ የመጽናት ምክንያት ስለኾነ ነው። ስለዚህ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዳለ “ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” ስለዚህ ፈጥነን በክርስቶስ ፊት በመቅረብ የኃጢአት ይቅርታችንን ልናገኝ ያስፈልጋል እንጂ፥ በኃጢአታችን ጽንተን በመኖር ወደ ባርነታችን ልንመለስ አያስፈልግም።